ንጉሰ ነገስት ሐይለስላሴ I
2022
ቀዳማዊ ፡ ዓፄ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ (ቀ.ኃ.ሥ.) ከጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፫ እስከ መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. ፡ የኢትዮጵያ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ነበሩ። ተፈሪ ፡ መኰንን ፡ ሐምሌ ፲፮ ፡ ቀን ፡ ፲፰፻፹፬ ዓ.ም. ፡ ከአባታቸው ፡ ከልዑል ፡ ራስ መኰንን ፡ እና ፡ ከእናታቸው ፡ ከወይዘሮ ፡ የሺ ፡ እመቤት ፡ ኤጀርሳ ፡ ጎሮ ፡ በተባለ ፡ የገጠር ፡ ቀበሌ ፡ ሐረርጌ ፡ ውስጥ ፡ ተወለዱ። በ፲፰፻፺፱ ፡ የሲዳሞ ፡ አውራጃ ፡ አገረ ፡ ገዥ ፡ ሆኑ። በ፲፱፻፫ ዓ.ም. ፡ የሐረርጌ ፡ አገረ ፡ ገዥ ፡ ሆኑ። የሐረርጌ ፡ አገረ ፡ ገዥ ፡ ሲሆኑ ፣ በጣም ፡ ብዙ ፡ ሺህ ፡ ተከታዮች ፡ ነበሩዋቸውና ፡ ልጅ ፡ እያሱን ፡ ከእንደራሴነት ፡ በኅይል ፡ እንዳያስወጡ ፤ እያሱም ፡ ተፈሪን ፡ ከሐረር ፡ አገረ ፡ ገዥነት ፡ እንዳይሽሯቸው ፡ የሚል ፡ ስምምነት ፡ ተዋዋሉ። ዳሩ ፡ ግን ፡ እያሱ ፡ ሃይማኖታቸውን ፡ ከክርስትና ፡ ወደ ፡ እስልምና ፡ እንደቀየሩ ፡ የሚል ፡ ማስረጃ ፡ ቀረበና ፡ ብዙ ፡ መኳንንትና ፡ ቀሳውስት ፡ ስለዚህ ፡ ኢያሱን ፡ አልወደዱዋቸውም ፡ ነበር። ከዚህም ፡ በላይ ፡ እያሱ ፡ ተፈሪን ፡ ከሐረር ፡ ከአገረ ፡ ገዥነታቸው ፡ ለመሻር ፡ በሞከሩበት ፡ ወቅት ፡ ስምምነታቸው ፡ እንግዲህ ፡ ተሠርዞ ፡ ተፈሪ ፡ ደግሞ ፡ ለወገናቸው ፡ ከስምምነቱ ፡ ተለቅቀው ፡ በዚያን ፡ ጊዜ ፡ እሳቸው ፡ እያሱን ፡ ከእንደራሴነት ፡ አስወጡ። እንግዲህ ፡ በ፲፱፻፱ ፡ ዓ.ም. ፡ መኳንንቱ ፡ ዘውዲቱን ፡ ንግሥተ ፡ ነገሥት ፡ ሆነው ፡ አድርገዋቸው ፡ ተፈሪ ፡ ደግሞ ፡ እንደራሴ ፡ ሆኑ። ከዚህ ፡ ወቅት ፡ ጀምሮ ፡ ተፈሪ ፡ በኢትዮጵያ ፡ ውስጥ ፡ ባለሙሉ ፡ ሥልጣን ፡ ነበሩ። በመስከረም ፳፯ ፡ ቀን ፡ ፲፱፻፳፩ ፡ ዓ.ም. ፡ የንጉሥነት ፡ ማዕረግ ፡ ተጨመረላችው። በ፲፱፻፳፪ ዓ.ም ፡ ንግሥት ፡ ዘውዲቱ ፡ አርፈው ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ሆኑና ፡ ጥቅምት ፳፫ ፡ ቀን ፡ ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. ፡ ብዙ ፡ የውጭ ፡ ልዑካን ፡ በተገኙበት ፡ ታላቅ ፡ ሥነ-ሥርዓት ፡ ቅብዓ ፡ ቅዱስ ፡ ተቀብተው ፡ እሳቸውና ፡ ሚስታቸው ፡ እቴጌ ፡ መነን ፡ ዘውድ ፡ ጫኑ።